Get Adobe Flash player

ሰኔ 29, 2012 ዓ.ም.

Error
  • JLIB_APPLICATION_ERROR_COMPONENT_NOT_LOADING


 

(Amharic Font download)

የርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረትና እድገት በአጭሩ

 

መግቢያ

ደብረ ሰላም  ቅድሰት ማርያም  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን በእነ መጋቤ ካህናት ከሃሊ ወንዳፈረው  አነሳሽነት እ.ኤ.አ በ1987 ዓ/ም ተመሰረተች።

ስትመሰረት አንድ ካህንና ሁለት ዲያቆናት ብቻ የነበሩባት ይህች የደብረ ሰላም ቅድሰት ማርያም ቤተ ክርሰቲያን  ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች በመምጣት በአሁኑ ሰዓት  ከሃያ የሚበልጡ ካህናትና ዲያቆናት  አገልግሎት ይሰጡባታል።  የተገልጋዮች የምዕመናንም ብዛት እንዲዚሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ በሳምንት እስከ 3000 ምዕመናን የሚጎበኟት ታላቅ ደብር ለመሆን በቅታለች።

የደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ ወደ ጊዜ በምታሳየው ለውጥ፣ በንብረትና በምዕመናን ብዛት እንዲሁም በመንፈሳዊና በማህብራዊ አገልግሎት ስፋት ልቃ በመገኘቷ እ.ኤ.አ በሴምፕቴምበር 2001  ዓ/ም በብፁዕ አቡነ አቡነ ይስሐቅ እና በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ “የርዕሰ አድባራት” ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚል ስያሜ  አግኝታለች።

አስተዳዳራዊ መዋቅር

የርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን  በአሜሪካ ፌዴራል መንግስት  በግብር አዋጅ (501)(ሲ) (3) መሠረት የተቋቋመች በመሆኗ በየሁለት ዓመቱ በምልዓተ ጉባኤው በሚመረጡ ከካህናትና ከምዕመናን በተወጣጡ አስራ ሁለት የባለ አደራዎች ቦርድ ትመራለች።

ቤተ ክርስቲያናችን ተጠሪነቱ ለባለ አደራዎች ቦርድ የሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን የዕለት ከዕለት ሥራ የሚያከናወንና የሚቀቆጣጠር የቤተ ክርስቲያን አለቃ (ዋና አስተዳዳሪ) አላት። የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና አስተዳዳሪ (አለቃ) በሥራቸው ከሚገኙ ሁለት መምሪያዎች ጋር ማለትም የመንፈሳዊ አገልግሎት ጉዳይ መምሪያ እና የአስተዳደር አገልግሎት ጉዳይ መመሪያ ጋር በመሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊና ማሕበራዊ አገልግሎት ያከናውናሉ።

የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታ መስፋፋት

በዋሽንግቶን ዲሲ ኮሎምቢያ መንገድ ላይ በኪራይ ቤት የተጀመረው የዚህች ቤተ ክርሰቲያን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመሄዱ በካህናትና በምዕምናን ብርታት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከ65000 ሰኩየር ጫማ በላይ ይዞታ ገዝታ አገልግሎቷን በመስጠት ላይ ትገኛች።

  • እ.ኤ.አ በ1997 ዓ/ም አሁን የምትገለገልበትን 1350 ቡካናን መንገድ በመባል የሚታወቀው ንብረት ተገዛ፣ የቤተ ክርሰቲያኒቱም አገልግሎት ወደዚሁ አድራሻ በዚሁ ዓመት በፊብሯሪ ወር ተዛወረ፣
  • እ.ኤ.አ 1998 ዓ/ም አዋሳኝ የሆነውን 14ኛው መንገድና ቡካናን መንገድ ላይ የሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ቦታ ተገዛ፣ አሁንም በመኪና ማቆሚያነት እንገለገልበታለን፣
  • እ.ኤ.አ በ2002 ዓ/ም 14ኛውና ዲኬተር መንገድ ላይ የሚገኘውን የመኖሪያ ቤት ተገዛ፣
  • እ.ኤ.አ በ2004 ዓ/ም በፊት የበረዶ ቤት  የነበረው በአርካንሳስ መንገድ የሚገኘው ቦታ ተገዛ፣ ይህንን ንብረት በአርካንሳስ በኩል ያለውን ለመኪና ማቆሚያና ለደጀ ሰላም፣ በ14ኛ መንገድ ላይ ያለውን ለትምህርት ቤትና ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንገለገልበታለን፣ 
  • 2009 ዓ/ም በተለያዩ ጊዚያት የተገዙ ይዞታዎች በአንድ ተጠቃለው 1350 Buchanan St. NW, Washington, DC 20011  የሚል የአድራሻ ስያሜ ተሰጠው።  ይህ አድራሻ አሁን ቤተ ክርሰቲያነቱ የምትገለገልበት አድራሻ ነው።

 

መንፈሳዊና ማሕበራዊ አገልግሎቶች

ይህች ቤተ ክርስቲያን በዚህች ጭንቀት በበዛባት ምድር ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው እረፍት እንዲያገኙና ከካህናት የምክር አገልግሎት እንዲሰጣቸው ሳምንቱን ሁሉ በሯ ክፍት የሆነችና ከጧት እስከ ማታ ካህን የሚገኝባት ቤተ ክርስቲያን ናት።

ዘወትር እሁድ፣ የእመቤታችን እለት ወር በገባ በ21ኛው ቀን፣ የአባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት እለት ወር በገባ በ24ኛው ቀን እና በዓመት በዓላትጊዜ የቅዳሴ አገልግሎት፣ በዓበይት በዓላት፣ በዓቢይ ጾም፣ በወርኃ ጽጌ፣ በጾመ ፍልሰታ፣ በንግሥ በዓላት እና በሌሎች በዓላት ጊዜ የማኅሌት/የሰዓታት አገልግሎት፣ ዘወትር ከልደታ እስከ ሥላሴ የነግህ ጸሎት አገልግሎት ያለማቋረጥ ይሰጣል።

በቤተ ክርሰቲያናችን በሳምንት ሦስት ቀናት  ማክሰኞ፣ ረቡዕ እና ዓርብ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ  የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ይሰጣል።

በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከ200 በላይ ሕጻናት ክርስትና ይነሳሉ። የሥርዓተ ተክሊል እና ጸሎተ ፍትሐት አገልግሎትም እንዲሁ ይፈጸማል።

ቤተ ክርስቲያናችን ዓመታዊ በጀት መድባ ኢትዮጵያ የሚገኙ ገዳማትንና የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን ትደጉማለች። በከባድ ችግር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖችም  ምዕመናንን በማስተባበር  ትርዳለች።

ቤተ ክርስቲያናችን በዓመት ከ50,000.00 ዶላር በላይ በመመደብ ሕጻናትና ወጣቶች በቃለ እግዚአብሔር እና በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉና ኢትዮጵያውያን ልጆች በሁሉም መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ  ለማድረግ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሕጻናትና ወጣቶች ከመንፈሳዊ ትምህርቱ በተጨማሪ የአማርኛ ቋንቋና ባህላቸውን በማስተማር ትውልድን በማነጽ ላይ ትገኛለች።

የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ የሒሳብ መዝገብ አያያዝና የአሜሪካ ሕግ በሚያዘው መሠረት ግልጽና ለቁጥጥር አመች በሆነ መልኩ በአካውንቲንግ ሶፍትዌር በሒሳብ ባለሙያዎች ይሠራል።  ሒሳቡም በየዓመቱ በውስጥና በውጭ ኦዲተሮች ይመረመራል።

የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎቶች በቀጥታ በኢንተርኔትና በስልክ በማስተላለፍ በአካባቢያቸው ቤተ ክርስቲያን ለማያገኙ፣ ከአቅማቸው በላይ በሆነ ችግር ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት ለማይችሉ ሁሉ በአሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎቱን እንዲሳተፉ ይደረጋል።

በአጠቃላይ በእግዚአብሔር እርዳታ፣ በእመቤታችን አማላጅነት እንዲሁም በካህናትና በምዕመናን ጸሎት፤ በመንፈሳዊና በማህበራዊ አገልግሎት፣ በካህናትና በምንዕመናን ቁጥር፣ በንብረትና በሀብት ብዛት አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ደርሳለች። አሁንም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ምንነት ለምዕራቡ ዓለም የሚያሳይ ታሪካዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት ጉዞ ጀምራለች። ይህ ሕንጻ ቤተ ክርሰቲያን ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ከመንፈሳዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ ለኢትዮጵያውያንና ለአካባቢው ማህበረሰብ ልዩ ልዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ስለሚሰጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህችን ቤተ ክርስቲያን በሙያው፣ በገንዘቡና በእውቀቱ ድጋፍ እንዲያደረግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን

 

እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅ

 

ሊቀ ማዕምራን ዶ.ር አማረ ካሳዬ
የርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ

Copyright DSK-Mariam © 2016. All Rights Reserved.